1 Samuel 19

ሳኦል ዳዊትን ለመግደል ያደረገው ሙከራ

1ሳኦል ዳዊትን እንዲገድሉት ለልጁ ለዮናታንና ለባልሟሎቹ ነገራቸው። ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድደው ነበር፣ 2እንዲህ ሲል አስጠነቀቀው፤ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ አጋጣሚ እየፈለገ ነው፤ ነገ ጧት ተጠንቀቅ፤ ወደ አንድ መደበቂያ ቦታም ሂድ፤ በዚያም ቈይ። 3እኔም እወጣና አንተ ባለህበት ዕርሻ ከአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም አነጋግረዋለሁ፤ የተረዳሁትንም እነግርሃለሁ።”

4ዮናታን ለአባቱ ለሳኦል ስለ ዳዊት እንዲህ ሲል መልካም ነገር ተናገረ፣ “ንጉሥ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አያድርግ፤ እርሱ አልበደለህም፤ ያደረገውም ነገር በእጅጉ ጠቅሞሃል። 5ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን የገደለው በገዛ ሕይወቱ ቈርጦ ነው። እግዚአብሔር ለመላው እስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ። ታዲያ እርሱን በከንቱ በመግደል ዳዊትን በመሰለ ንጹሕ ሰው ላይ ለምን በደል ትፈጽማለህ?”

6ሳኦልም ዮናታንን ካዳመጠው በኋላ፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም” ብሎ ማለ።

7ስለዚህም ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ የተባባሉትን ሁሉ ነገረው፤ ወደ ሳኦልም አመጣው፤ ዳዊትም እንደ ቀድሞው በፊቱ ቆመ።

8እንደ ገና ሌላ ጦርነት ተነሣ፤ ዳዊትም ወጥቶ ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው፤ ከፊቱም እስኪሸሹ ድረስ እጅግ መታቸው።

9ነገር ግን ሳኦል ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ
ወይም የሚጐዳ
መንፈስ መጣበት፤ ዳዊት በገናውን ይደረድር ነበር፣
10ሳኦልም ከግድግዳው ጋር ሊያጣብቀው ጦሩን ወረወረበት፤ ነገር ግን ዳዊት ዘወር በማለቱ ሳኦል የወረወረው ጦር በግድግዳው ላይ ተሰካ። በዚያች ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ።

11ሳኦልም የዳዊትን ቤት ከብበው በማለዳ እንዲገድሉት ሰዎችን ላከ። የዳዊት ሚስት ሜልኮል ግን፣ “ሕይወትህን ለማትረፍ በዚህች ሌሊት ካልሸሸህ፣ በነገው ቀን ትገደላለህ” ብላ አስጠነቀቀችው። 12ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አሾልካ አወረደችው፣ እርሱም ሸሽቶ አመለጠ። 13ከዚያም ሜልኮል የጣዖት
በዚህና በቍጥር 13 ላይ ዕብራይስጡ ተራፊም ይላል።
ምስል ወስዳ በዐልጋው ላይ አጋደመችው፤ በራስጌውም የፍየል ጠጕር አኖረች፤ በልብስም ሸፈነችው።

14ሳኦል ዳዊትን እንዲይዙት ሰዎች በላከ ጊዜ ሜልኮል፣ “እርሱ ታሟል” አለቻቸው።

15ሳኦልም ሰዎቹ ዳዊትን እንዲያዩት መልሶ ላካቸው፤ እርሱም፣ “እገድለው ዘንድ ከነዐልጋው አምጡልኝ” አላቸው። 16የተላኩትም ሰዎች በገቡ ጊዜ እነሆ፤ የጣዖት ምስሉ በዐልጋው ላይ ተጋድሞ በራስጌውም የፍየል ጠጕር ተደርጎለት ነበር።

17ሳኦልም ሜልኮልን፣ “እንዲህ አድርገሽ ያታለልሽኝ፣ ጠላቴ እንዲያመልጥ የሰደድሽው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት።

ሜልኮልም፣ “ ‘እንዳመልጥ እርጂኝ፤ አለዚያ እገድልሻለሁ’ አለኝ” ብላ መለሰችለት።

18ዳዊት ሸሽቶ ካመለጠ በኋላ፣ ወደ አርማቴም ወደ ሳሙኤል ሄደ፣ ሳኦል ያደረገበትን ሁሉ ነገረው። ከዚያም እርሱና ሳሙኤል ወደ ነዋት ሄደው ተቀመጡ። 19ለሳኦልም፣ “እነሆ፤ ዳዊት በአርማቴም በምትገኘው በነዋት ተቀምጧል” ብለው ነገሩት። 20ስለዚህ ዳዊትን እንዲይዙ ሰዎችን ላከ፤ ይሁን እንጂ፣ የነቢያትም ጉባኤ በሳሙኤል መሪነት ትንቢት ሲናገሩ ባዩ ጊዜ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል ሰዎች ላይ ወረደ፤ እነርሱም እንደዚሁ ትንቢት ተናገሩ። 21ሳኦልም ይህ በተነገረው ጊዜ ሌሎች ሰዎች ላከ፤ እነርሱም ትንቢት ተናገሩ፤ ሳኦል ለሦስተኛ ጊዜ ሰዎች ላከ፣ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። 22በመጨረሻም፣ እርሱ ራሱ ወደ አርማቴም ሄደ፤ ከዚያም በሤኩ ወዳለው ትልቅ የውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ እንደ ደረሰ፣ “ሳሙኤልና ዳዊት የት ናቸው?” ሲል ጠየቀ።

አንድ ሰውም “በአርማቴም በምትገኘው በነዋት ዘራማ ናቸው” ብሎ ነገረው።

23ስለዚህ ሳኦል በአርማቴም ወደምትገኘው ወደ ነዋት ዘራማ ሄደ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱም ላይ ደግሞ ወረደ፤ ወደ ነዋት እስኪደርስ ድረስም ትንቢት እየተናገረ ተጓዘ። 24እርሱም ልብሱን አውልቆ፣ በሳሙኤልም ፊት ደግሞ ትንቢት ተናገረ፤ በዚህ ሁኔታም ቀኑንና ሌሊቱን በሙሉ ራቍቱን ተጋደመ። ሕዝቡ፣ “ሳኦልም ደግሞ ከነቢያት እንደ አንዱ ሆኖ ተቈጠረ?” ያለው በዚህ ምክንያት ነው።

Copyright information for AmhNASV